በወላይታ ሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ”ቅይጥ የማስተማር ሥነ-ዘዴ” (Blended Learning) የኢኖቬቲቭ ፔዳጎጂ የአሰልጣኞች ሥልጠና ተጀመረ።
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም
በወላይታ ሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የተዘጋጀውና የማስተማር-መማር ሂደቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል የተባለው የ”ኢኖቬቲቭ ፔዳጎጂ” (Innovative Pedagogy) የአሰልጣኞች ሥልጠና ዛሬ በይፋ መጀመሩ ተገልጿል።
ይህ ሥልጠና በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የEASE (Ethiopian Eduction for Employability) ፕሮጀክት እና ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ የመጀመሪያውን ምዕራፍ በኦንላይን (Online) ለ15 ቀናት በስኬት ሲሰጥ ቆይቶ፣ የዛሬውን ሁለተኛ ምዕራፍ ፊት-ለፊት (Face-to-Face) ሥልጠና ለተከታታይ 5 ቀናት የሚቆይ ይሆናል።
የሥልጠና መድረኩን በንግግር በይፋ ያስጀመሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ ባስተላለፉት መልዕክት፡- በአሁኑ ወቅት የቴክኒክና ሙያ ተቋሞቻችንን ብቁ፣ ተወዳዳሪና ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር አብረው የሚራመዱ ለማድረግ የሰልጣኞችን አቅም መገንባት አማራጭ የሌለው ተግባር ነው። ዛሬ የጀመርነው የ’ቅይጥ ማስተማር ሥነ-ዘዴ’ (Blended Learning) ሥልጠና አሠልጣኞቻችን ባህላዊውን የማስተማር ዘዴ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት ዕውቀትን በብቃት እንዲያስተላልፉ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
በኦንላይን የተሰጠውን 15 ቀናት ሥልጠና አጠናቃችሁ ዛሬ ለፊት-ለፊት ሥልጠና የተገኛችሁ አሰልጣኞች፣ ከዚህ መድረክ የምታገኙትን የኢኖቬቲቭ ፔዳጎጂ ዕውቀትና ክህሎት በቀጥታ ወደ ክፍለ-ክፍል በመውሰድ የተቋሙን የሥልጠና ጥራት ወደ ላቀ ደረጃ እንድታሸጋግሩ አደራ እላለሁ። ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉት ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር EASE ፕሮጀክት እና ለፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።”
ይህ የኢኖቬቲቭ ፔዳጎጂ ሥልጠና አሰልጣኝ መምህራን ዘመናዊና ተለዋዋጭ የሆኑ የማስተማር ስልቶችን እንዲላመዱ፣ የሠልጣኞችን የተግባርና የፈጠራ ክህሎት እንዲያሳድጉ እና የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ጥራት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ ያለመ ነው።
የወላይታ ሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ
ጥራት ያለው ስልጠና ለተግባራዊ እውቀት!










